የኦሮሚያ-ክልል-በአዲስ-አበባ-ላይ-ያለው-ልዩ-መብት-አዋጅ-Edited-PDF
የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት መግቢያ ላይ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መጪው የጋራ እድላችን መመስረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበላቸው፣
ሕገ-መንግስቱ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች እውቅና የሰጠ፣ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የህዝቦች ተጠቃሚነት ከተረጋገጠላቸው ብሔሮች መካከል አንዱ የኦሮሞ ህዝብ በመሆኑ፣
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት በአንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (5) የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል አካል በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለውን ልዩ ጥቅም እንደሚጠበቅለት በመደንገጉ፣
የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ዝርዝር በሕግ እንደሚወሰን በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (5) ስለሚደነግግና ይህንን ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 55 ንዑስ አንቀፅ (1) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፣
ክፍል አንድ:- ጠቅላላ ድንጋጌ
1/ አጭር ርዕስ
ይህ አዋጅ “የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ህገ-መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር ____/2009” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
2/ ትርጓሜ
በዚህ አዋጅ ውስጥ የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም የሚሰጠው ካልሆነ በስተቀር ፡-
1) “ሕገ-መንግስት” ማለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ- መንግስት አዋጅ ቁጥር 1/1987 ማለት ነው፡፡
2) “ክልል” ማለት የኦሮሚያ ክልል ማለት ነው፡፡
3) “መንግስት” ማለት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ነው፡፡
4) “ጨፌ ኦሮሚያ” ማለት የኦሮሚያ ክልል የህግ አውጭ አካል ማለት ነው፡፡
5) “ልዩ ጥቅም” ማለት በሕገ መንግስቱ ውስጥ እውቅና ያገኙ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ አስተዳደራዊ፣ የልማት፣ የፖለቲካ፣ የአካባቢ ደህንነት፣ የንብረት መብቶች የመሳሰሉትን በልዩ ሁኔታ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ላይ የሚያገኘዉ ጥቅም ማለት ነው፡፡
6) “አስተዳደር” ማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማለት ነው ፡፡
7) “የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች” ማለት የአዲስ አበባ ከተማ ከመመስረቱ በፊት ጀምሮ ነባር ነዋሪ የነበሩ ወይም አሁንም በከተማው ነዋሪ የሆኑ ኦሮሞዎች ማለት ነው፡፡
8) “ሰው” ማለት ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም ሕጋዊ የሰውነት መብት ያለው አካል ነው፡፡
3/ የተፈጻሚነት ወሰን
ይህ አዋጅ በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዉስጥ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡
4/ የፆታ አገላለጽ
በዚህ አዋጅ በወንድ ፆታ የተገለፀው የሴት ፆታንም ይጨምራል፡፡
5/ ስያሜ
1) የከተማው ስም ፊንፊኔ ከአዲስ አበባ ጋር እኩል መጠሪያ ይሆናል፡፡
2) የከተማው ሕጋዊ ስም በፅሁፍ ፊንፊኔ/አዲስ አበባ ተብሎ ጥቅም ላይ መዋል ይኖርበታል፡፡
6/ ወሰን
1) የከተማው ወሰን የከተማው አስተዳደርና የክልሉ መንግስት በሚያደርጉት የጋራ ስምምነት ይወሰናል፡፡ የወሰን ምልክትም ይደረግበታል፡፡
2) በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1) በተደነገገው መሰረት የተቀመጠውን የወሰን ምልክት ከተደረገበት በኋላ በማናቸውም ምክንያት መስፋት የማይቻል ሲሆን ወሰኑንም ክልሉ እና አስተዳደሩ የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡
3) ይህ አዋጅ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ወሰን ተከልሎ ምልክት መደረግ ይኖርበታል፡፡
7/ የስራ ቋንቋ
የከተማው አስተዳደር የስራና ኦፊሴላዊ ቋንቋ አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ነው፡፡
8/ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መብት
1) በከተማው አስተዳደር ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት እና በሌሎች የሀገሪቱ ሕጎች የተከበሩ መብቶች በከተማው ውስጥ የመጠቀም ሙሉ መብት አላቸው፡፡
2) የከተማ አስተዳደሩም ይህንን መብት የማክበር ግዴታ ይኖርበታል፡፡
ክፍል ሁለት:- የኦሮሚያ ክልል በከተማው አስተዳደሩ ላይ የሚኖረው ልዩ ጥቅሞች
9/ ጠቅላላ
በዚህ አዋጅ ውስጥ የተጠቀሱት ዝርዝር የክልሉ መብቶችና ልዩ ጥቅሞች በህገ- መንግሥቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (5) ላይ የተገለፀውን አጠቃላይ አነጋገር የሚገድበው አይሆንም፡፡
10/ የልዩ ጥቅሙ መርሆዎች
1) የከተማ አስተዳደሩ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎችና ዕቅዶች የከተማው ነዋሪ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ሕገ መንግስታዊ መብቶች የሚያስከብር መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡
2) የከተማ አስተዳደሩ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎችና ዕቅዶች የነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆችን ጥቅሞችና ፍላጎቶች ግምት ውስጥ ያስገባና መብቶቻቸውን የሚያስከብር መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
3) የመስተዳድሩ ምክር ቤት ከክልሉ መብቶችና ጥቅሞች ጋር በሚያያዙ ጉዳዮች ላይ በሚሰጠው ውሣኔ የክልሉን ጥቅሞች ከግምት ውስጥ በማስገባት ይወስናል፡፡
11/ ስለ አስተዳደራዊ ጥቅሞች
1) በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪ የሆነው የኦሮሞ ተወላጆች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብት ይኖራቸዋል፡፡
2) በከተማው መስተዳደር ም/ቤት ውስጥ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች እንደ ከተማው ነዋሪ ያላቸው ውክልና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከምክር ቤት ወንበር 25% የማያንስ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ብቻ የሚወከሉበት መቀመጫ ይኖራቸዋል፡፡
3) በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (2) ላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ውክልና በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች፣ የሥራ አስፈፃሚውና የዳኝነት አካል ውስጥ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡
4) በኦሮሚያ የመንግስታዊና ህዝባዊ ድርጅቶች መስሪያ ቤቶች ውስጥ ወይም ጉዳዮች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወንጀል ሰርተው ወደ 4 ፊንፊኔ/አዲስ አበባ በመምጣት የሚደበቁትን ተጠሪጣሪ ወንጀለኞች የክልሉ ፖሊስ፣ አቃቤ ህግና ፍርድ ቤቶች የመመርመር፣ የመያዝና የመቅጣት ሙሉ መብት ይኖራቸዋል፡፡
5) በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (4) የተደነገገ ቢኖርም፣ በፊንፊኔ/አዲስ አበባ የተፈፀሙ ከክልሉ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ከፌዴራልና ከከተማ አስተዳደሩ የፍትህና የፀጥታ አካሎች ጋር በትብብር መስረት ይኖርባቸዋል፡፡
6) ፊንፊኔ/አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ ሆና ታገለግላለች፡፡
ስለ ማህበራዊ የአገልግሎት ጥቅሞች
1) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለተለያዩ መንግሥታዊ፣ ሕዝባዊና የልማት ማህበሮች ቢሮዎች፣ ክልሉ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶቹን ለስብሰባ አደራሾች፣ የኮሚኒቲ ማዕከላትና ለሌሎች ሕዝባዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ህንፃዎችና ፋሲሊቲዎች የሚገነባበት በቂ መሬት ክልለሉ ከሚፈለገው አከባቢ ከከተማ አስተዳደሩ ከሊዝ ነፃ የማግኘት ጥቅሙ ይጠበቅለታል፡፡
2) ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የኦሮሞ ተወላጆች የመኖሪያ ቤት በከተማ አስተዳደሩ ከሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በ15% ቅድሚያ የማግኘት ወይም የመከራየት መብት ይኖራቸዋል፡፡
3) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትና የከተማው ነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆች አደባባዮች፣ ማዕከላት፣ አዳራሾች፣ ስታዲየሞች፣ ሜዳዎች…ወዘተ አገልግሎት ማግኘት ሲፈልጉ ቅድሚያ የመጠቀም ሙሉ መብት ይኖራቸዋል፡፡
4) በከተማው አስተዳደር ውስጥ ነዋሪ ለሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በአፋን ኦሮሞ የሚያስተምሩ ት/ቤቶች በመስተዳድሩ ወጪ ተሰርተው ትምህርት እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡
5) የከተማ አስተዳደሩ ከከተማው ዳሪ ላይ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የጤና አገልግሎት በቅርብ እንዲያገኙ የጤና ተቋማትን እንዲያስፋፋ ይደረጋል፡፡
6) የክልሉ ቢሮዎችና ሠራተኞች የሚጠቀሙባቸው የመኖሪያ ቤቶች የሚሆን የመብራት፣ ውኃ፣ መንገድ፣ ስልክና ወዘተ የመሰረተ ልማቶች አገልግሎቶች እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
7) በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ዙሪያ ለሚኖረው ሕብረተሰብ ልዩ ልዩ የማህበራዊ አገልግሎቶች እንደ መንገድ፣ ትራንስፖርት፣ መብራት፣ ውኃ፣ ስልክና የመሳሰሉትን በማቅረብ የፊንፊኔ 5 ዙሪያ ኦሮሚያ ዞን ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
8) ለከተማው መስተዳድር የመጠጥ ውሃ አገልግሎት በክልሉ ከሚገኙ የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር ውሃ የሚገኝ በመሆኑ የመጠጥ ውሃ አገልግሎቱ የሚገኝበትና የአገልግሎቱ መስመር የሚያልፍባቸው የክልሉ ከተሞች እና ቀበሌዎች የውሃ አቅርቦት ዝርጋት በመስተዳድሩ ወጭ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው፡፡
9) የከተማ መስተዳድር ለከተማው ህዝብ የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች በመስተዳድሩ አዋሳኝ ለሚኖረው የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ሊዳረሱ የሚችሉ ሲሆን ነዋሪዎቹ በተመሳሳይ ሁኔታ የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ የመሆን መብት ይኖራቸዋል፡፡
10)ከተማ አስተዳደሩ የከተማ አዋሳኝ የሆኑ የክልሉ ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች ላይ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች እንዳይከሰቱ የመጠበቅና የመከላከል፤ ተከስተው ከተገኙም ጉዳቱን የመቀነስ ሃላፊነት አለበት፡፡
11)የከተማው አስተዳድር ለከተማው ህዝብ ከሚያቀርባቸው አገልግሎቶች ጋር በተያያዙ የልማት ሥራዎችን በክልሉ መንግስት ጋር በመመካከርና በመስማማት ሊፈፅም ይችላል፡፡
13/ ስለ ባህላዊና ታሪካዊ ጥቅሞች
1) በከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች መጠሪያ ወይም ስያሜዎች በጥንት ስሞቻቸው እንዲጠሩና ተዛብተው እየተጠሩ ያሉት ስሞች እንዲስተካከሉ ይደረጋል፡፡
2) የከተማ አስተዳደሩ የኦሮሞ ሕዝብ ብሔራዊ ማንነት የሚያንፀባርቅ አሻራ በከተማው ውስጥ በቋሚነት እንዲኖር ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር የተያያዙ ታሪካዊ ክስተቶች ወይም በኦሮሞ ብሄራዊ ጀግኖች ስም መታሰቢያዎች እንዲኖሩ የመንግስት ተቋማት ህንፃዎች፣ አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ አይሮፕላን ማረፊያ፣ ሠፈሮች እና የመሳሰሉት በስማቸው የመሰየም ሃላፊነት አለበት፡፡
3) በከተማ አስተዳሩ ወጪ በተቋቋሙ የሬድዮና የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያዎች ከከተማው የሚተላለፉ ፕሮግራሞች ለአፋን ኦሮሞ የአየር ጊዜ የመመደብ ግዴታ አለበት፡፡
4) በፊንፊኔ/አዲስ አበባ የሚኖረው የዛሬውና መጪው ትውልድ የፊንፊኔን ታሪክ በተዛበ መልኩ ሳይሆን ኦሮሞዎች ይኖሩበት የነበረች ጥንታዊ መሬታቸው እንደነበረችና በኃይል ተገፍተው ወደ ዳር በመገፋታቸው ቁጥራቸው እየተመናመነ መሄዱንና ወደ አናሳነት መቀየራቸውን ህዝቡ እንዲያውቅና እውቅና እንዲሰጥ የከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ስርዓት፣ በሚዲያ፣በህዝባዊ መድረኮችና በመሳሰሉት የመስራት ግዴታ ይኖራዋል፡፡
5) በመስተዳድሩ ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የታሪክ ማስተማሪያ መፃሕፍት ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ የፊንፊኔ/አዲስ አበባ የጥንት ነባር ሕዝብ መሆኑን አዲሱ ትውልድ እንዲገነዘብ ይደረጋል፡፡
6) በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች የማንነቱ ዋና መገለጫ የሆኑት ታሪኩን፣ እምነቱን፣ ቋንቋውን፣ ባህላዊ እሴቶቹን የመጠበቅ፣ የማሳደግና ስራ ላይ የማዋል መብቱን የከተማ አስተዳደሩ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡
7) በከተማው ውስጥ የሚገኙ ሙዚያሞች፣ የባህል ማዕከላት፣ የሲኒማና ትያትር ቤቶች እና ፓርኮች የኦሮሞ ባህላዊ እሴቶች፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ወግ ሊያንሰራሩበት የሚችሉ ስልቶችን በመቀየስ የድጋፍ እርጃዎችን የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡
8) በከተማው መስተዳድር ውስጥ በሚገኙ ሙዚየሞች ውስጥ የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ፣ ባህል፣ ወግ የሚያንፀባርቁ ቅርፆችንና መጽሐፎች እንዲሟሉና እንዲኖሩ መስተዳድሩ ከክልሉ ጋር በመመካከር የመስራት ግዴታ አለበት፡፡
14/ ስለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች
1) በከተማው የሚኖረው የኦሮሞ ተወላጅ ከመሬቱ ያለመፈናቀል ሙሉ ዋስትና አለው፡፡
2) በከተማው አስተዳደር ውስጥ በልማት ምክንያት ለሚነሱ የኦሮሞ አርሶ አደሮች በተነሱበት አከባቢ በዘላቂነት የመቋቋም መብት አላቸዉ፡፡
3) ለልማት ተነሺ መሆኑ ሲረጋገጥ በቂ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ማሳወቅ፣ በካሳ ግመታ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግና የወቅቱን የገበያ ዋጋ ያገናዘበ በቂ የካሳ ክፍያና ምትክ ቦታ ለተነሽው አርሶ አደርና ለቤተሰቡ በተነሱበት አከባቢ እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
4) በልማት ምክንያት የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች የተከፈላቸውን ካሳ በዘላቂነት መጠቀም እንዲችሉ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ስራ ላይ እንዲውሉ ይደረጋል፡፡
5) በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (2) ስራ ላይ ለማዋል እንዲቻል የከተማ አስተዳደሩ ራሱን ያቻለ ይህን ስራ የሚሰራ ተቋም በማቋቋም መደገፍና መከታተል ይኖርበታል፡፡
6) ቀደም ሲል በልማት ምክንያት ከይዞታቸው ተነስተው ለተለያዩ ማብበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ተገቢውን መረጃ በማሰባሰብና በማደራጀት መልሰው እንዲቋቋሙ ይደረጋል፡፡
7) ከተማ አስተደዳደሩ ለቋንቋ አገልግሎት፣ ለጋራ ምክር ቤቱ፣ ቦታን ከሊዝ ውጭ የሚሰጥ፣ የመኖሪያ ቤት ቅዲሚያ የሚሰጥ፣ የት/ቤቶች ግንባታና ማስፋፋት፣ የውሃ አቅርቦት ለአከባቢው ህዝብ በነፃ የሚሰጥ፣ ለኦሮሞ ተወላጆች ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ መስፋፋትና መንከባከብ የሚሰራ በመሆኑ ምንጫቸው ከክልሉ ሆኖ ወደ መስተዳድሩ በሚገቡ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ለኢንዱስትርና ለፋብሪካዎች የሚውሉ ጥሬ እቃዎች፣ ለመጠጥ ውሃና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ይጠቀማል፡፡
8) በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚመረቱ የአርሶ አደር ወይም ማህበራት ምርቶች ፊንፊኔ/ አዲስ አበባ ውስጥ የገበያ ቦታ ከሊዝ ነፃ ያገኛሉ፡፡
9) የከተማ ነዋሪ የሆነው የኦሮሞ ተወላጆች በንግድና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የስራ መስኮች ውስጥ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲያድግ የድጋፍ ርምጃዎችን በመውሰድ ነባሩን የኦሮሞ ህዝብ በከተማው ከሚኖረው አብዛኛው ማህበረሰብ ጋር ፍትሃዊ የሐብት ክፍፍል እንዲኖር የከተማ አስተዳደሩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ግዴታ አለበት፡፡
15/ ስለ አካባቢ ደህንነት ጥቅሞች
1) መስተዳድሩ ከከተማው የሚወጡትን ደርቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች የሚያስከትሉትን ጉዳት የአካባቢ ብክለት ቁጥጥርን አስመልክቶ በወጡ ሕጐች መሠረት የማስቀረት ግዴታ አለበት፡፡
2) ከከተማው አስተዳደር የሚወጡ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች ወደ ክልሉ እንዳይለቀቁ ማድረግ፣ ተለቆ ከተገኘ በሰው፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ አከባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና ብክለት መተበቅና መከላከል፣ መስተዳድሩ ወደ ክልሉ በተጣሉ ወይም በፈሰሱ ቆሻሻዎች ምክንያት በሰው፣ በእንስሳት፣ በመሬት፣ በአከባቢና በአየር ብክለት ላይ ለደረሰው ጉዳት በቂ ካሳ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡
3) መስተዳድሩ ከከተማው የሚያወጣቸው ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎችን የማከም ወይም መልሶ የመጠቀም ስልት በማቀድ መስተዳድሩ ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
4) በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ዙሪያ ለሚገኙት ቀበሌዎች ወንዞችና የተፈጥሮ ሀብቶች አስፈላጊውን እንክብካቤ የማድረግ ግዴታ ይኖርበታል፡፡
16/ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መብቶች
1) የክልሉ መንግስት በከተማ አስተዳደሩ በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎችና ዕቅዶች የኦሮሞ ተወላጆችን ጥቅሞችና ፍላጎቶች ግምት ውስጥ ያስገባና መብቶቻቸውን የሚያስከብር መሆኑን አስተያየት እና የማሻሻያ ሐሳብ የማቅረብ መብት ይኖረዋል፡፡
2)ክልሉ ከተማውንና ክልሉን በሚያስታሳስሩ ጉዳዮች ላይ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶችን በማመንጨት ለአስተዳደሩ ምክር ቤት የማቅረብ ስልጣን ይኖረዋል፡፡
3)የክልሉ መንግስት የዚህን አዋጅ ማሻሻያ ሀሳብ በማመንጨት ለኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማቅረብ መብት ይኖረዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ይህን አዋጅ ለማሻሻል ሲፈልግ የክልሉ መንግስት አስተያየት መጠየቅ ይኖርበታል፡፡
4)የኢ.ፌ.ደ.ሪ. መንግሥት የሚኒስትሮች ም/ቤት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም ደንብ ከማውጣቱ በፊት የክልሉን አስተያየት ጠይቆ በደንቡ ውስጥ አስተያየቱ እንዲያካተት ማድረግ ይኖርበታል፡፡
5)የከተማ አስተዳደሩ የነዋሪ ኦሮሞዎችንና የክልሉን መብትና ጥቅም ሊነኩ የሚችሉ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎችና ዕቅዶች በአስተዳደሩ ምክር ቤትና በጋራ ምክር ቤት በውይይት ከስምምነት ላይ ካልደረሰ ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡
ክፍል ሶስት:- ስለ የኦሮሞ ብሔራዊ ጉባዔ መቋቋም
17/ ስለመቋቋም
1) የኦሮሞ ብሔራዊ ጉባዔ በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች የሚወከሉበት የኦሮሞ ብሔራዊ ጉባዔ ከዚህ በኋላ “ጉባዔ“ ተብሎ የሚጠራ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡
2) የኦሮሞ ብሔራዊ ጉባዔ አባላት በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ የሚሳተፉበት ምርጫ በአገሪቱ የምርጫ ሕግ መሰረት ይፈጸማል፡፡
3) ጉባዔው ቋሚ ጽ/ቤት፣ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እና ሙያተኞች ይኖሩታል፡፡
18/ የጉባዔው ሥልጣንና ተግባር
የኦሮሞ ብሔራዊ ጉባዔ ከዚህ በታች የተመከለቱትን ሥልጣንና ተግባር ይኖሩታል፡፡
1) በከተማው ውስጥ የኦሮሞ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ እንዲጠበቅ፣ እንክብካቤ እንዲያገኝ ፖሊሲና ሕግ ያወጣል፤ የከተማ አስተዳደሩም የማስፈፀም ግዴታ ይኖራዋል፡፡
2) በከተማው አስተዳደር ውስጥ ነባሪ የቦታ ስያሜዎች ተመልሰው እንዲያንሰራሩ ሕግ ያወጣል፡፡
3) በከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ውስጥ የሚወከሉ የኦሮሞ ተወላጅ ተወካዮችን አባላት ይመርጣል፡፡
4) ኦሮሞዎችን ወክለው የከተማ አስተዳደሩን የሚመሩ የሥራ ሃለፊዎች ከንቲባ እና ሌሎች የካቢኔ አባላትን ተጠቁመው በምክር ቤቱ እንዲጸድቅ ያስደርጋል፡፡
5) በአዋጁ ውስጥ የተደነገጉ የከተማ አስተዳደሩ ነዋሪ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መብቶችና ጥቅሞች በትክክል ተግባራዊ መሆናቸውን ይከታተላል፡፡
6) ጉባዔውን የሚመራ አፈ ጉባዔ፣ ምክትል አፈጉባዔና ሌሎች ሃላፊዎችን ይመርጣል፡፡
7) ጉባዔው ስራውን በአግባቡ ለመፈፀም እንዲያስችለው ልዩ ልዩ አደረጃጀት ሊኖረው ይችላል፡፡
8) ጉባዔው የአሰራር ስርዓት መመሪያ ሊያወጣ ይችላል፡፡
19/ የጉባዔው ዋና መሥሪያ ቤት
1) የጉባዔው ዋና መሥሪያ ቤት አድራሻ ፊንፊኔ/አዲስ አበባ ነው፡፡
2) ጉባዔው እንደአስፈላጊነቱ በከተማው የአስተዳደር እርከኖች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሊኖሩት ይኖራዋል፡፡
20/ አርማ
ጉባዔው የራሱ አርማ ይኖረዋል::
21/ በጀት
የከተማው አስተዳደሩ ምክር ቤት ለጉባዔው ሥራ የሚያስፈልገውን በጀት ከጉባዔው በሚቀርብለት ጥያቄ መሰረት የመመደብ ግዴታ አለበት፡፡
22/ የጉባዔው የሥራ ዘመን
የጉባዔው የሥራ ዘመን 5 ዓመት ሆኖ የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ምርጫ ተካሂዶ በአዲስ መልክ ሲዋቀሩ ይኸውም ጉባዔ በአዲስ መልክ ይዋቀራል፡፡
ክፍል አራት:- ስለ የጋራ ምክር ቤት መቋቋም
23/ የጋራ ምክር ቤት መቋቋም
የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ውስጥ ስላለው ልዩ ጥቅምን አስመልክቶ የወጡትን ሕጎች ተግባራዊነት የሚከታተልና የሚያስፈፅም ከክልሉ ወይም ከጉባዔውና አስተዳደሩ የተውጣጣ የጋራ ምክር ቤት ከዚህ በኋላ “የጋራ ምክር ቤት“ ተብሎ የሚጠራ በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡
24/ የጋራ ምክር ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤት
1) የጋራ ምክር ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤት አድራሻ ፊንፊኔ/አዲስ አበባ ነው፣
2) የጋራ ምክር ቤቱ በከተማው የአስተዳደር እርከን በየትኛውም ስፍራ የተለያዩ አደረጃጀትና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሊኖረው ይችላል፤
25/ አርማ
የጋራ ምክር ቤቱ የራሱ አርማ ይኖረዋል::
26/ የጋራ ምክር ቤቱ ሥልጣንና ተግባር
የጋራ ምክር ቤቱ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባር ይኖሩታል፡፡
1) የጋራ ምክር ቤቱ በዚህ አዋጅ የተደነገጉ ጥቅሞች፣ በምክር ቤቱና ጉባዔው የሚወጡ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ዕቅዶችና ሕጎች መፈፀማቸውን ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፣
2) በክልሉና በአስተዳሩ የጋራ ጉዳዩች ላይ ተጨማሪ ጥናቶች እንዲደረጉ ይደረጋል፤ ሲፀድቁም ተግባራዊ እንዲሆኑ ይደረጋል፣
3) የጋራ ም/ቤቱ በክልሉና በአስተዳሩ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም አስመልክቶ የወሰናቸውን ውሣኔዎች የሚቃረን ውሣኔ ማንኛዉም አካል መወሰን አይችልም፡
4) የጋራ ምክር ቤቱ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በአፋን ኦሮሞ የሚማሩበትን ትምህርት ቤት መስተዳድሩ መክፈቱን፣ መገንባቱን፣ የመምህራንና ለመማር ማስተማር የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች መሟላቱን ይከታተላል ያስፈፅማል ፡፡
5) የጋራ ምክር ቤቱ በልማት ምክንያት ለሚነሱ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መብትን ያስጠብቃል በዘላቂነት መቋቋም እንዲችሉ የመልሶ ማቋቋሙን ሥራ ይከታተላል ያስፈፅማል፡፡
6) የጋራ ምክር ቤቱ ስራውን በአግባቡ ለመፈፀም እንዲያስችለው ልዩ ልዩ አደረጃጀት ሊኖረው ይችላል፡፡
7) የጋራ ምክር ቤቱን የአሰራር ስርዓት መመሪያ ሊያወጣ ይችላል፡፡
27/ የጋራ ምክር ቤቱ አመሠራረት
1) 44 አባላት ያሉት በክልሉ ወይም ከጉባዔውና ከአስተደዳሩ በተውጣጡ አባላት ምክር ቤቱ ይቋቋማል፡፡
2) 22 አባላት ከክልሉ ወይም ከጉባዔው ይወከላሉ፡፡
3) 22 አባላት ከአስተዳደሩ ምክር ቤት ይወከላሉ፡፡
4) የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ከጉባዔው ከተወከሉት አባላት መካከል ይሆናል፡፡
5) የጋራ ምክር ቤቱ ም/ሰብሳቢ በአስተዳደሩ ምክር ቤት ከተወከሉት አባላት መካከል ይሆናል፡፡
6) ምክር ቤቱ ቋሚ ጽ/ቤት፣ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እና ሙያተኞች ይኖሩታል፡፡
28/ በጀት
የከተማው አስተዳደሩ ምክር ቤት ለጋራ ምክር ቤቱ ሥራ የሚያስፈልገውን በጀት ከጋራ ምክር ቤቱ በሚቀርብለት ጥያቄ መሰረት የመመደብ ግዴታ አለበት፡፡
29/ የጋራ ምክር ቤቱ የሥራ ዘመን
የጋራ ምክር ቤቱ የሥራ ዘመን 5 ዓመት ሆኖ የፊነፊኔ/አዲስ አበባ ምክር ቤት እና የጉባዔው ምርጫ ተካሂዶ በአዲስ መልክ ሲዋቀሩ ይኸውም የጋራ ምክር ቤቱ በአዲስ መልክ ይዋቀራል፡፡
ክፍል አምስት:- ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
30/ መተባበርና የመፈፀም ግዴታ
1) ይህን አዋጅ እና አዋጁን ተከትሎ የሚወጡትን ደንቦችና መመሪያዎች ሥራ ላይ ለማዋል ማናቸውም ሰው ወይም አካል የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡
2) የከተማ አስተዳደሩ እና የአስተዳደሩ መንግስታዊ አካላት በሙሉ አዋጁን የመፈፀም ግዴታ አለባቸው፡፡
31/ የአዋጁን አፈፃፀም ስለመቆጣጠር
1) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ጨፌ ኦሮሚያ ይህን አዋጅና በአዋጁ መሰረት የሚወጡትን ደንቦችና መመሪያዎች በትክክል ስራ ላይ መዋላቸውን የመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት ይኖራቸዋል፡፡
2) የኢ.ፌ.ደ.ሪ. መንግሥት የሚኒስትሮች ም/ቤት እና ክልላዊ መንግስቱ ይህን አዋጅና በአዋጁ መሰረት የሚወጡትን ደንቦችና መመሪያዎች በትክክል ስራ ላይ መዋላቸውን የመከታተልና የመደገፍ ሥልጣንና ኃላፊነት ይኖራቸዋል፡፡
32/ ተፈፃሚነት ስለማይኖራቸው ህጐች
ይህን አዋጅ ጋር የሚቃረን ማንኛውም ሕግ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ፣ መመሪያ፣ የአሠራር ልምዶች ወይም ውሳኔዎች በዚህ አዋጅ ውስጥ የተደነገጉ ጉዳዮች በሚመለከት ተፈፃሚነት አይኖራቸውም፡፡
33/ ደንብና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን
1) የኢ.ፌ.ደ.ሪ. መንግሥት የሚኒስትሮች ም/ቤት ይህን አዋጅ ለማስፈፀም ደንብ ሊያወጣ ይችላል፡፡
2) ጉባዔው እና የአስተዳደሩ ምክር ቤት ይህን አዋጅና በአዋጁ መሰረት የሚወጣውን ደንብ ለማስፈፀም መመሪያ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡
34/ አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ አዋጅ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡
ፊንፊኔ/አዲስ አበባ ……….. ቀን 2009 ዓ.ም
ሙላቱ ተሾመ(ዶ/ር)
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት